ኢትዮጵያ ምዕራባውያን የከፈቱባትን ጦርነት ድል እንደምታደርግ አምናለሁ ስትል የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጇ ሙምቢ ሴራኪ (ዶ/ር) ገለጸች

ሙምቢ ሴራኪ (ዶ/ር)

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶቿን ዳግም ድል እንደምታደርግ አምናለሁ ስትል ኬንያዊቷ የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጅ ሙምቢ ሴራኪ (ዶ/ር) ገለጸች፡፡

ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያሳዩት ያለውን ጣልቃ ገብነት እና ያልተገባ ጫና በምታዘጋጃቸው ፕሮግራሞቿ ትኮንናለች።

ኢትዮጵያ ለብቻዋ ከምዕራባዊያን ኃይሎች ጋር ጦርነት ላይ ነች፣ በአፍሪካ ምድር ድሮም ክብሯን በወራሪ ሳታስደፍር የኖረችው ኢትዮጵያ ዛሬም ነጮቹን ዳግም ድል እንደምታደርግ አምናለሁ ነው ያለችው።

ሊቢያ ላይ ወረራ የፈጸመው ቲም ኦባማ ጆ ባይደንን ተከትሎ ነጩ ቤተ መንግስት ገብቷል ያለችው ሙምቢ ሴራኪ (ዶ/ር) ይሄ ትግል በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ ዘመቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን ኢላማ ያደረገ መሆኑን ተናግራለች፡፡

የቴሌቪዥን ሾው አዘጋጇ ግብጽ አሜሪካን የመሰሉ አገራትን ሳይቀር ከጎኗ ይዛ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ማሸነፍ ሲሳናት አሸባሪዎችን አስታጥቃ ቀጣናው እንዳይረጋጋ እየሰራች መሆኑን አስታውቃለች።

አፍሪካውያን እንዲነቁና ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም መጠየቋን ከማኅበራዊ ትስስር ገጿ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያሰራጩትን ሀሰተኛ ዘገባ በማጋለጥና ትክክለኛ መረጃዎችን በማጋራት ኢትዮጵያን ማገዝ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች።