ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል – የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

ሰኔ 30/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ ሰላም ያስፈልጋታል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው የሰላም ሩጫ ውድድር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ አትሌቶችና ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የሰላም ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ ሰላም ያስፈልጋታል፤ የሰላም ሩጫው ዋና ዓላማም የሰላም ፍላጎታችንን ከፍ አድርገን ለማሳየት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች እያሳካቻቸው ያሉትን ስኬቶች ለማስቀጠል፤ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከንቲባ አዳነች በበኩላቸው የከተማችን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ የተጠበቀው ሕዝብን ያሳተፈ የሰላም ስራ በመሰራቱ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህን ሰላም አስጠብቆ ለመዝለቅ ሁሉም ሰው እያበረከተ ያለውን ድርሻ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዛሬው ዕለት የሩጫ ውድድሩ በተለያዩ የክልል ከተሞችም ተካሂዷል።