ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ቀድሞ ለመፍታት በቅንጅት እየሰራች ነው – የሰላም ሚኒስቴር

የሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው

ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ቀድሞ ለመከላከልና ለመፍታት እንደ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን (ኢጋድ) ካሉ የቀጠናው ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኗን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በኢጋድ ስር ከሚገኘው ሲዋን ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “በኢትዮጵያ በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ አሰጣጥ” ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው እንደገለጹት ኢትዮጵያ መላ አፍሪካውያንን በማስተባበር የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ድርጅቶችን በመመስረት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች።

አሁን ላይ እንደ ኢጋድ ካሉ ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዓለም ላይ በኢኮኖሚና ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚከሰቱ ቀውሶችን ለመከላከል እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በድርቅ፣ ጎርፍ፣ አንበጣና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል የሚቻልበት አሰራር በመዘርጋት የጋራ ተጠቃሚነትን እየተገበረች እንደምትገኝ አስረድተዋል።

ወይዘሮ ፍሬዓለም በማያያዝ ኢትዮጵያን በማፍረስ የምንፈልገውን እናሳካለን ብለው የሚያስቡ ሃይሎች የብሄር ግጭትን በመፍጠርና በመደገፍ ተጠምደው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“በውጭ የሚገኙ ሃይሎችና የሀገር ውስጥ ተባባሪዎቻቸው ግንባር ፈጥረው የሚንቀሳቀሱት የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌትና 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዳይካሄድ በማለም ነው” ብለዋል።

“የኛ ችግር የሌሎች አጎራባች ሀገራት ችግር ነው” ያሉት ወይዘሮ ፍሬዓለም እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

“መንግስት የለውጡን መምጣት ተከትሎ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማሻሻያ በማካሄድ የሀገሪቱን ብልጽግና ለማስቀጠል እየሰራ ነው” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር

“ለውጡን ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የህዳሴውን ግድብና ምርጫውን በሰላም ማካሄድ አስፈላጊ ቢሆንም የውጭ ሃይሎች ጫና ቀላል አይደለም” ብለዋል።

“በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የያዘችው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ህዝቦች የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም አካል እውነታውን መገንዘብ እንዳለበት አመልክተዋል ።

በኢጋድ ስር የሚገኘው ሲዋን እያካሄደ ያለው የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያና ምላሽ መድረክ በምርጫውና በግድቡ ሙሌት የሚስተዋሉ ችግሮችን መርምሮ እውነቱን ለዓለም ህዝብ በማሳወቅ ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በሲዋን የግጭት ተንታኝ ዶክተር ሰንዳይ አንጎማ በበኩላቸው በኢጋድ አባል ሀገራት እኤአ በ2002 የተቋቋመው ሲዋን የግጭት መከላከልና የሰላም ግንባታ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የቀጠናው ሀገራት በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች የመፍረስ አደጋ እየተጋረጠባቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል” ብለዋል።

የችግሩን መሰረታዊ ጉዳይ ተገንዝቦ በዘላቂነት ለመፍታት መረጃ በመሰብሰብ፣ በመተንተንና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለኢጋድና ሌሎች አካላት በማቅረብ ድርጅታቸው እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

“የቀጠናው ሀገራት በጋራ በመሆን በአነስተኛ ወጪ፣ የሰው ሃይልና በተቀናጀ አመራር በመስራት እንደ ኮቪድ 19፣ የአንበጣ መንጋ፣ ድርቅ፣ ግጭትና ሌሎች ክስተቶችን መከላከል ይችላሉ” ብለዋል።