ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሽብር ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገች

ጥቅምት 25/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ የሽብር ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሚውሉ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶችን ለሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስረክቧል።

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሶማሊያ በመገኘት በሽብር ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሚውሉ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶችን ለሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ማስረከቡ ተገልጿል፡፡

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከጤና ሚኒስቴር የተወጣጡ የልዑካን ቡድኑ አባላት፤ የአልሸባብ የሽብር ቡድን ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት  19 ቀን 2015 ዓ.ም በፈጸመውና ከ100 በላይ ሰዎች በተገደሉበት የሽብር  ጥቃት  የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በሶማሊያ ሞቃዲሾ በመገኘት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን አመልክተው ለሶማሊያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትንና ብርታትን ተመኝተዋል፡፡

የልዑክ ቡድኑ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሽብር ጥቃቱ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ላጋጠማት ሶማሊያና ለሀገሪቱ ዜጎች ያላቸውን ወገንተኝነት ለመግለጽ እንዲሁም የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ  የሽብር ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያርጉ ጥሪ በማቅረባቸው ድጋፉ መደረጉን  የጠቆመው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ የሶማሊያ የጤና  ሚኒስትር አሊ ሐጂ አደም (ዶ/ር) ድጋፉን መቀበላቸውን አመልክቷል፡፡

ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ፣ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት የብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሑሴን ሼይክ ሞዓሊም እና ከውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ዶ/ር ሞሐመድ አሕመድ ጋር በመገናኘት ሐዘናቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡

ምክትል ዳይሬክተሩ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይደገሙም ኢትዮጵያ  ከሀገሪቱ ጸጥታና ደኅንነት አካላት ጋር የምታደርገውን የትብብርና የአጋርነት ሥራዎች አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡