ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለባት ተረጋገጠ


ሰኔ 6/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለባት በዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኦዲት ባለሙያዎች ተረጋገጠ፡፡

የተባበሩት መንግስታት አካል በሆነው የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኦዲት ባለሙያዎች የተደረገው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት ኦዲት ውጤት ይፋ ሆኗል።

የኦዲት ስራው መጠናቀቁን ተከትሎ የኦዲት ስራውን ያስተባበረው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት መምሪያ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ ውጤቱን አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ አቪየሽን ደህንነት ኦዲት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቢቆይም ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርትን እ.አ.አ በ1946 ከአዲስ አበባ-ካይሮ በተደረገው ታሪካዊ በረራ የጀመረች ሲሆን ለዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (አይካኦ) አባል ከሆኑ እና በአቪዬሽን ዘርፍ ቀዳሚ ሀገራት አንዷ መሆኗን አመላክተዋል።

ባለፉት ዓመታት መንግስት የአቪየሽን ዘርፉን ጠንካራና ለደህንነት ችግር ተጋላጭ ያልሆነ አስተማማኝ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱንም አብራርተዋል።

የአቪየሺን ደህንነቱ የተጠበቀ ተቋም ከመፍጠር አንፃር ከፍተኛ ሪፎርም የተደረገ በመሆኑ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛልም ብለዋል።

ከሰሞኑ በዘጠኝ ኦዲት ዘርፎች በከፍተኛ ባለሙያዎች ጥልቅ ዳሰሳዎች መደረጉን ገልፀው የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በኤርፖርቶችና በህግ ማዕቀፍ ሁለንተናዊ ቅኝቶች መደረጋቸውን አስረድተዋል።

የባለሙያዎች ኦዲት ውጤቱም ኢትዮጵያ ምንም አይነት የአቪዬሽን ደህንነት ስጋት እንደሌለባት ያረጋገጠ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

ምንም አይነት የአቪዬሽን ዘርፍ ደህንነት ስጋት እንደሌለ መረጋገጡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት እና ለኢትዮጵያ ትልቅ ድልና ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል።

ግኝቱ የኢትዮጵያን ቀደምት ስምና ታሪኳን የሚመጥን ነው፤ ይህም በአቪዬሽን ዘርፉ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ትልቅ ዋስትና እንደሆነና የቱርዝም እድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ደህንነቱ የተጠበቀ የአቪየሽን ደህንነት የመገንባት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

ዝርዝር የኦዲት ውጤቱን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በኩል ይፋ እንደሚደረግም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዓለም አቀፍ ኦዲት በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት /አይሲኤኦ/ የኦዲት ባለሙያዎች አማካኝነት ከግንቦት 26/2016 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

በሳራ ስዩም