ኢትዮጵያ በዶራሌህ ወደብ የቀንድ ከብት ተርሚናልን ለመጠቀም ከጂቡቲ ጋር ስምምነት ተፈራረመች

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በጂቡቲው ዶራሌህ ወደብ የቀንድ ከብት ተርሚናልን መጠቀም የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከጂቡቲ ጋር መፈራረሟን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

ስምምነቱን የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን ከጅቡቲው የግብርና፣ የውኃ፣ የዓሣ፣ የቀንድ ከብት እና የባህር ሀብት ሚኒስትሩ ሞሐመድ አሕመድ አዋሌህ ጋር ተፈራርመዋል።

የጂቡቲው የዶራሌህ ወደብ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን የቀንድ ከብት ተርሚናል አንዱ ነው።

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን በመግባቢያ ስምምነቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብት ቀዳሚ ሀገር እንደመሆኗ አሁን የተፈረመው ስምምነት ይህንን ሀብት በአግባቡ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬን እንድታገኝ ያስችላታል ብለዋል።

ተርሚናሉ ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ሥራውን እንዲሠራ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት መሆኑንም ገልጸዋል።

የጂቡቲው የግብርና፣ የውኃ፣ የዓሣ፣ የቀንድ ከብት እና የባህር ሀብት ሚኒስትሩ ሞሐመድ አሕመድ አዋሌህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና ጂቡቲ መካከል ያለው የንግድ ትሥሥር እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የጂቡቲ መንግሥት አሁን ለተፈረመው የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተግባራዊነት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ኤምባሲውን ጠቅሶ የዘገበው ኢብኮ ነው።