“ኢትዮጵያ ትጣራለች” በሚል በጎንደር የገቢ ማሰባሰቢያ ሲጀመር ባለሃብቱ ወርቁ አይተነው 50 ሚሊዮን ብር ቃል ገቡ

ኅዳር 19/2014 (ዋልታ) “ኢትዮጵያ ትጣራለች” በጎንደር ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር እየተካሄደ ነው።

የአገርን ኅልውና ለመታደግ ውድ ህይወታቸውን አስይዘው በግንባር ለተሰለፉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ለሆኑ ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለፋኖ፣ ለአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም በአሸባሪው የትሕነግ ቡድን ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የገቢ መሰባሰቢያ ፕሮግራም በጎንደር ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል ፡፡

አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በሦስት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ የአማራን ሕዝብ ለማጥፋት ቀን ከሌት ሲሰራ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን አሁን ላይም በሥልጣን ላይ እያለ ያልጨረሰውን በጦርነት ለማሳካት እየሞከረ መሆኑ ተነስቷል።

ሕወሓት የአማራን ዘር ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለመበተን ቆርጦ መነሳቱን የገለፁት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ የሽብር ቡድኑን ለመመከት የጎንደር ሕዝብ ለአገሩ ወታደር ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

አሁን በተጀመረው የገንዘብ ማሰባሰብ ግንባር ላይ የሚገኙት ባለሀብቱ ወርቁ አይተነው 50 ሚልዮን ብር ለመለገስ ቃል መግባታቸው ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን 71 ሚልዮን ብር ቃል ተገብቷል፡፡