ኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጀመረችውን ሂደት እንደግፋለን – ዓለም አቀፉ የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ

ሩፓክ ቻቶፓዲሂያይ

መስከረም 11/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጀመረችውን ሂደት እንደሚደግፉ የዓለም አቀፉ ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ ፕሬዝዳንት ሩፓክ ቻቶፓዲሂያይ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ፕሬዝዳንቱ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ የለውጥ ምህዋር ውስጥ እያለፈች መሆኗን ያደነቁት ፕሬዝዳንት ሩፓክ የለውጥ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ዓለም አቀፉ የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ በጎ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መልካም የሽግግር ሂደት ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው በሀገራዊ ምክክር ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረው ሂደት እንዲሳካ ፎረሙ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን በማጥበብና አንድነታቸውን በማጠናከር ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሀገራዊ ምክክር የሀገራትን ተሞክሮ የመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

በመሆኑም ዓለም አቀፉ የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ ለምክክሩ ስኬታማነት ጠቃሚ የሆኑ ልምዶችን በማካፈል ሂደት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ ጋር ያላትን ትብብርና ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ ዋና መቀመጫውን በካናዳ ያደረገ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ የፎረሙ አባል በመሆን እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡

ፎረሙ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት በኢትዮጵያ ቢሮ በመክፈት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል።