ኢትዮጵያ ችግሮቿን ለመፍታት በምታደርገው ጥረት የጃፓን አድናቆት

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እናደንቃለን ሲሉ ገለጹ።

አምባሳደሯ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ጉዞ በፈጣን ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ጃፓንን ጨምሮ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ መምጣቱም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገርን ሉአላዊነት የማስከበር ሂደቱ ከገጠማት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉም አምባሳደሯ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የተለያዩ ችግሮች በማደግ ላይ ያሉም ሆነ ያደጉት አገራትን ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተና ታልፈዋለች ብለዋል።

አምባሳደሯ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማት፣ የፍቅርና አንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።

በአዲሱ ዓመትም ችግሮች ሁሉ ተወግደው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ ልማት፣ ፍቅርና አንድነት እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ግንኙነቷን ይበልጥ የምታጠናክረበት እንደሚሆንም እምነቴ የፀና ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ጃፓን የትብብር ግንኙነት ከ90 ዓመታት በላይ የዘለቀና አሁንም በጠንካራ ወዳጅነት የቀጠለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።