ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን መጠቀሟ ከኢኮኖሚ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት ያሉ አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ዕድሎቿን ማስፋቷ ኢኮኖሚውን ከመደገፉም ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ያሏትን እድሎች የማስፋት ተግባራት እያከናወነች ነው።

ኢትዮጵያ በወጪና ገቢ ንግድ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ የታጁራ፣ በርበራና ፖርት ሱዳን ወደቦችን እየተጠቀመች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

እያደገ የመጣውን የገቢና ወጪ ንግድ መሸከም የሚያስችል ተጨማሪ ወደብ መጠቀም እንዳስፈለገ ጠቁመው፤ የላሙ ወደብን ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነ ተናግረዋል።

አገሪቷ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም በመቻሏ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን እንድታሰፋ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ ወጪን በመቀነስም ለልማት ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም በዚህ ዓመት በታጁራ ወደብ ብቻ ከ700 ሺህ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰልና ከ200 ሺህ ቶን በላይ ካርጎ መግባት በመቻሉ በጂቡቲ ወደብ ላይ ይወሰድ የነበረውን ጊዜ እንዳሳጠረ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ወደብ ካላቸው አገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት አብሮ ለመልማትና የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ከወደብ አገልግሎቱ በተጨማሪም በመሰረተ ልማት ስራዎችም መንገዶች ወደሌሎች የቀጣናው አገሮች መሸጋገሪያ እንዲሆኑ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ይበልጥ የሚጠናከርበት ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት ከካይሮ እስከ ኬፕታውን የሚዘረጋው የመንገድ አካል የሆነው ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።