ኢትዮጵያ አሜሪካ ስለእኔ እያወራች ያለችው ከሌላ አገር ጋር ነው አለች

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመነጋገር ሌላ ወደሌሎች አገራት ማሄዷን ኢትዮጵያ ተቸች፡፡

ዛሬ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ከመነጋገር ይልቅ በተደጋጋሚ ከሌሎች አገራት ጋር መወያየትን መርጣለች ብለዋል።

ዋልታ አሜሪካ እየሄደችበት ያለውን ለኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውይይት 3ኛ አገር የመፈለግ ተደጋጋሚ ተግባር በተመለከተ ማሳያዎችን ጠቅሶ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመወያየት ኬንያ፣ ሴኔጋልና ናይጄሪያ የነበሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከትናንት በስቲያ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በድጋሚ መወያየታቸው ይታወቃል፡፡

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጀፍሪ ፊልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ወደግብፅ፣ ቱርክና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በማቅናት መወያየታቸውም ይታወሳል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና “አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየት ከፈለለገች እኛ ሁሌም ዝግጁ ነን፤ በእኛ ጉዳይ ከእኛ ጋር መወያየት አለባቸው” ሲሉ ነው የአሜሪካን አቋም የተቹት፡፡