ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) አየርላንድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከሚያጓድሉ ተግባራት የማትቆጠብ ከሆነ ኢትዮጵያ ከሀገሪቷ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጤን እንደምትገደድ አሳሰበች፡፡
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጉዳዩ ዙሪያ ለሀገሪቱ ውጪ ጉዳይ እና መከላከያ ሚኒስትር ሳይመን ኮቨኒ በጻፉት ደብዳቤ ሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ላይ የተመሰረት ግንኙነት እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት ያለቸውን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ጎን በመተው አየርላንድ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ያላትን ተለዋጭ አባልነት እና የአውሮፓ ህብረት አባልነቷን በመጠቀም እየፈጸመች ያለችው ደባ ኢትዮጵያ ያልጠበቀችው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ በሀገሪቱ እያበበ የመጣው ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያስደነገጠው አሸባሪው ህወሓት ወታዳራዊ ኃይል ሲያሰለጥን ቆይቶ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል።
ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭት መቀስቀሱን እና ግጭቱን ለማስቆምም የፌዴራል መንግስት የወሰዳቸውን ጥረቶች ውድቅ በማድረግ ጥቃት መፈጸሙን እንደቀፀጠለ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ያመለከቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ህብረት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ሁሉ መቀበሉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በግጭቱ ወቅት ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ወገኖችን በመጠየቁ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው አብራርተዋል። ለሀገሪቱ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አየርላንድ እነዚህ በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እና በሀገሪቱ እየተካሄዱ ያሉትን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደገፍ እንደሚገባት ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አየርላንድ ግን አባል በሆነችባቸው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እና የአውሮፓ ህብረትን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጻረሩ ተግባራት ላይ መጠመዷን ኮንነዋል።
አየርላንድ በአፍራሽ ድርጊቷ በመቀጠል በህዝብ ይሁንታ የተመረጠውን መንግስት ከመደገፍ ይልቅ በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ተለዋጭ መቀመጫ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ግፊት እያደረገች መሆኗን ነው ያስረዱት። ይህ አይነቱ ደርጊት አሸባሪውን ህወሓት የሚያበረታ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው አብራርተዋል፡፡
አየርላንድ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ እየፈፀመች ካለችው ጥቃት በተጨማሪ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይሻሻል ጋሬጣ መሆኗንም በደብዳቤውቸው አውስተዋል።
አየርላንድ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከሚጎዱ ተግባራት እንድትታቀብ ያሳሰቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ለማደስ ፍላጎት እንዳላትም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግንኙነቱን ለማሻሻል ያደረገቻቸው ሙከራዎች እስካሁን ፍሬ አለማፍራታቸውንም በማስታወስ አየርላንድ በኢትዮጵያ ልክ ለግንኙነቱ መሻሻል ፍላጎት እንዳለት እንደማይታወቅ አብራርተዋል።
በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊቀጥል የሚችለው አየርላንድ በደብዳቤው ውስጥ ለተዘረዘሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማጥቃት ተግባር በምትሰጠው ምላሽ ላይ እንደሚመሰረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳስበዋል።