የካቲት 17/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የነበሯቸውን ትብብሮች እና ውሎች በአዲስ የትግበራ ምዕራፍ ለማስቀጠል ተስማሙ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የሩሲያ ፌዴሬሽን ፓርላማ ሴናተር ኢጎር መሮዞቭ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሚኒስትሩ የአገራቱ ታሪካዊ ግንኙነት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚረጋግጥ መልኩ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር ኢጎር መሮዞቭ በበኩላቸው በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በስማርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና ኒውክለርን ለሰላም በመጠቀም ረገድ፣ በፋርማሲ ቴክኖሎጂ፣ በንግድ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የሁለትዮሽ አገራዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ሩሲያ ያላትን አቅም ለማካፈል እንደምትፈልግ ገልፀዋል፡፡
ሴናተር ኢጎር ሚኒስትር በለጠና አመራራቸው በሞስኮ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት እንዲያደርጉ የጋበዙ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በመጭው ሰኔ የሚካሄደው ዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ሚኒስትሩ እንዲገኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡