ኢትዮጵያ እና ሩስያ ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር ተስማሙ

ጥር 29/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ሩስያ በተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎችም ባለብዙ ግንኙነት መድረኮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር መስማማታቸውን አስታወቁ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳኖቭ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው ፈርጀ-ብዙ የሆነውን የሁለቱን አገራት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በኢነርጂ፣ መሰረተ ልማት፣ ግብርና እንዲሁም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በሁለቱ አገራት ትብብር ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከናወኑ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶችም ተወያይተዋል።
የጋራ ጥቅምን በሚመለከቱ ዋና ዋና ዓለም ዐቀፍ ሁነቶች ዙሪያም ሐሳብ የተለዋወጡ ሲሆን በዚህም በተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ባለብዙ ግንኙነት መድረኮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ግጭቶች እና ቀውሶችን በዓለም ዐቀፍ ሕግ እና የመንግሥታቱ ቻርተር አግባብ መፍታት እንደሚገባም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በ2022 ስለሚካሄደው 2ኛው የሩስያ-አፍሪካ ጉባኤ ዝግጅትም አንስተው መወያየታቸውን ነው ኢቢሲ የዘገበው፡፡
የሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳኖቭ የሩስያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪካ ልዩ ተወካይም ናቸው።