ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ በፖለቲካ፣ መከላከያ፣ በባህልና በቱሪዝም፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የተፈረመው ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው 3ኛው የኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ ነው።
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል እና በናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሁመር ዘናባ ፈርመውታል።
አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል የመግባቢያ ስምምነቱ በርካታ ዓመታት ያስቆጠረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የናይጄሪያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና አፍሪካ ኅብረት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ቪክቶር አዱኩን በሁለቱ አገራት መካከል በመከላከያ፣ በጤና፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪ፣ ባህል፣ ቱሪዝም፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ እንዲሁም አቪዬሽን መስክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን አስተዳደር እና አመራር በተለይም የወጣቶች ተሳትፎ በማሳደግ እና የፖን-አፍሪካዊነትን የሚዘክሩ ይዘቶችን ለማበልፀግ በሚቻሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ መካከል ያለውን ፀጋ በመጠቀም ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት እንዲዉል ያስችላል ተብሏል።
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በአፍሪካ ያለውን እምቅ የሰው ሀብት እና ገበያ በጋራ ማልማት እና መጠቀም በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ናቸው።
የ4ኛ የሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እ.ኤ.አ. 2024 አቡጃ ከተማ- ናይጄሪያ እንደሚካሄድ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW