ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፉ

ሐምሌ 1/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ መሪዎች በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ ማሳለፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጂቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑማር ጌሌ ቀደም ብለው ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከሰኔ 29-30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በጂቡቲ ይፋዊ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በኮቪድ፣ በውጭ እና በውስጥ ሁኔታዎች ሲቆራረጥ የቆየውን የሁለትዮሽ ውይይት ከቀድሞው የበለጠ በማጠናከር የጋራ የምጣኔ-ሃብት ትስስሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ በሁለቱም በኩል የታየውን ቁርጠኝነት አድንቋል፡፡

በመሆኑም የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ፣ ተምሳሌታዊና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገራት መሪዎች ቀደም ብለው በተወያዩት አግባብ መሰረት ሶስት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ተደርሷል።

የአትክልት እና ፍራፍሬ የዋጋ ተመንን በተመለከተ የሁለቱ አገራት መንግሥታት በሚያቋቁሙት የጋራ ኮሚቴ አማካኝነት የጂቡቲን ነባራዊ አሁናዊ ገበያ እና የሰፊውን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ የዋጋ ማሻሻያ እስከሚደረግ ድረስ ለጂቡቲ ብቻ ቀድሞ በነበረው ዋጋ እንዲቀጥል ተወስኗል።

በተጨማሪም ለ40 ዓመታት ሲሰራበት የቆየው ወደ ጂቡቲ የሚላከውን የጫት ምርት ታሪፍ ከፍ ለማድረግ ቀደም ብለው መሪዎቹ በተስማሙት መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የጂቡቲ አስመጪዎች የጫት ምርት የውጪ ሽያጭ ውል ምዝገባ መፈፀም ሳይጠበቅባቸው ምርቱን ማስገባት እንዲችሉ ወስነዋል፡፡

እንዲሁም የባህር አገልግሎት ክፍያዎች በሁለቱ አገራት መንግሥታት የሚመለከታችው አካላት በጋራ ምክክር ተደርጎበት ውሳኔ ላይ እስኪደርስ ማስተካከያው ሳይደረግ በነበረው ዋጋ እንዲቀጥል ከስምምነት መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።