ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ወካይ ድምጽ በነበራት የመሪነት ሚና ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 13/2016 (አዲስ ዋልታ) በቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ወካይ ድምጽ የነበራት የመሪነት ሚና ከትናንት እስከ ዛሬ በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ተወካይ እና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ እና የእስያ ፓስፊክ ዳይሬክተር ጀነራል አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በቻይና እና አፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጠናከር የወካይነት ሚናዋን እየተውጣች ነው ብለዋል፡፡

መድረኩም ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያሉ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ለመለየት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አማካሪ ሚኒስትር ያንግ ይሀንግ በበኩላቸው ቻይና እና ኢትዮጵያ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም በመመስረቱም ግንኙነታቸው ዘርፈ ብዙ እንዲሆን ያስቻለ ነው ብለዋል።

አማካሪ ሚኒስትሩ አክለውም እ.ኤ.አ በ2003 ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ማካሄዷን አንስተው ኢትዮጵያ በቻይና እና አፍሪካ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጎለብት የመሪነት ሚናዋን ተጫውታለች ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ትብብር በየአመቱ እያደገ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያም የግብርና ውጤቶችን ወደ ቻይና ገበያ በስፋት እየላከች መሆኑን አንስተዋል ።

መድረኩን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና በኢትዮጵያ የቻይና ኢምባሲ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተግኝተውበታል።

በመስከረም ቸርነት