መጋቢት 1/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የዓረብ ሊግ ያወጣውን መግለጫ እንደማትቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሊጉ በትናንትናው ዕለት ለአንድ ወገን የወገነ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወቅ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በዚህም የሕዳሴ ግድቡን የግንባታ ሥራና የውሃ ሙሌትን የማስተዳደር ስራ ለሚመለከታቸው ለተፋሰሱ የአፍሪካ ሀገራት ሊተው እንደሚገባ አንስቷል፡፡
ስለግድቡ ጉዳይ የሚመለከታቸው የተፋሰሱ ሀገራት እንዳሉ ለማስታወስ አንፈልግም ያለው መግለጫው ሊጉ መሰረታዊውን ዓለም አቀፍ ህግ ባላከበረ መልኩ የአንድ ሀገር ቃል አቀባይ ሆኖ እያገለገለ ነው ብሏል፡፡
የአፍሪካ ህብረትም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መርህን በመከተል ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅን ለማቀራረብ የሦስትየሽ ድርድር ሲያመቻች መቆየቱን ጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጫማሪም ግብፅ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ በራስ ወዳድነት በምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ድርድሩን ማዘግየቷን መግለጫው አመላክቷል፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የድርድር ሂደት በፅኑ እንደሚደግፍ ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም መንግስት በፈረንጆቹ መጋቢት 2015 በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል የተፈረመውን የስምምነት አዋጅ በመከተል የግድቡን ግንባታና ውሃ ሙሌት የሚቀጥል መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።