ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች – የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ


ሰኔ 10/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር በሁሉም ዘርፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 በሚካሄደውና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።

ከፎረሙ ጎን ለጎን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ዘርፍ ሚኒስትር ሊዩ ጂንቻዎ ጋር ባደረጉት ውይይት ቻይና በኢትዮጵያ ልማት ላይ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋር ሀገር መሆኗን አስረድተው በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች ባጋጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ቻይና የማይናወጥ አቋም ይዛ እያደረገች ላለው ድጋፍ አመስግነው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ወዳጅነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ባለው ብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲሳካ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና መንግስት ላደረጉት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ስትራተጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሊዩ ጂንቻዎን ጨምሮ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አመራሮች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

ሊዩ ጂንቻዎ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ማዕከል በመሆኗም ቻይና ከኢትዮጵያም አልፎ ከአፍሪካዊያን ጋር ለሚኖራት ትብብር ቁልፍ ሚና እንዳላት አስረድተዋል።

በመሆኑም የሁለቱን ሃገራት የቆየ ትብብር ከማሳደግ ባለፈ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱን በልምድ ልውውጥ፣ በስልጠና ፕሮግራሞች እና በአቅም ግንባታ ዘርፍም አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውንየሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ቻይና በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸው በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ትብብር የተገነባውን የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር በአብነት ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ በመጨረሻም በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው የቻይና አፍሪካ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ልዑካን እንዲገኝ ግብዣ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።