ኢትዮጵያ ከአግዋ አባልነት የታገደችበትን የአሜሪካ ውሳኔ ተቃወመች

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የቀረጥና ኮታ ነፃ ገበያ (አግዋ) አባልነት የታገደችበት ውሳኔ የተሳሳተ እና ለዜጎች ደኅንነት ዋጋ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ከአግዋ መሰረዙን ተከትሎ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አወጥቷል፡፡

እገዳው ከ200 ሺሕ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦችና ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ሴቶች ኑሮ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ብሏል፡፡

እንዲሁም በአቅርቦት ሰንሰለት ስነ ምኅዳር ውስጥ የሚሳተፉትን የአንድ ሚሊየን ሰዎች ህይወት እንደሚጎዳም አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ከአሜሪካ የሚጠብቁት አድሏዊ ያልሆነ የሰብኣዊ ድጋፍ አቅርቦት ቢሆንም ውጤቱ የንፁሃን ዜጎችን ምጣኔሃብታዊ ኅልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑንም መግለጫው አጽኦት ሰጥቷል፡፡

አሜሪካ ለድሃ አገራት የምትሰጠውን የቀረጥና ኮታ ነፃ እድል የባይደን አስተዳደር በተለይም ኢትዮጵያ ላይ ሲመጣ ከምጣኔ ሃብታዊ ማዕቀፉ አውጥቶ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያ አድርጎታል፡፡