ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በደቡብ ሱዳን የገንዘብና ፕላን ሚኒስትር አጋክ አቹል የተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሀገራቱ በኮሚሳ እና በኢጋድ እንዲሁም በዓለም ዐቀፍ ተቋማት መካከል በሚደረጉ ግንኙነቶች ማለትም በፋይናንስ እና በቴክኒክ በጋራ ለመሥራት ተሰማምተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ሁለቱ እህትማማች ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በተለይም ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ ንግድ እና ጉምሩክ ብሎም በመንገድና ኃይል አቅርቦት በትብብርና በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይም ለደቡብ ሱዳን አንድነትና ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሏን አሰተዋጽኦ እንደምታበረክትም ገልጸዋል፡፡
የገንዘብና ፕላን ሚኒስትር አጋክ አቹል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን በኢኮኖሚ፣ ሰላምና ደኅንነት እያደረገች ያለውን ሁሉን ዐቀፍ ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሜቴ መዋቀሩን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡