ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር 32 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያው ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር የ32 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርማለች፡፡

ድጋፉ በቀጣይ 5 ዓመታት ለሚተገበሩ 3 ፕሮጀክቶች የሚውል እንደሆነ በገንዘብ ሚኒስቴር በተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

ከፕሮጀክቶቹ አንዱ የገጠር ግብርና እሴት ሰንሰለት ማሻሻያ ሲሆን፣ ይህም ባለ አነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮችን ከገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ጋር በማገናኘት የሚፈፀም ይሆናል፡፡

ሁለተኛው ፕሮጀክት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የደን እና የአፈር ጥበቃ ስራ ሲሆን፣ ሶስተኛው እና የመጨረሻው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የተፋሰስ ልማት ማስተር ፕላን ዝግጅት እና የሸገር የወንዞች ተፋሰስ ልማት እና ፅዳት ነው ተብሏል፡፡