ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉት መረጃ የተለያዩ መሆናቸውን አሜሪካዊያን ጎብኝዎች ተናገሩ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታና በዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን የምትገለጸው ኢትዮጵያ እንዲሁም በመሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነታ እጅጉን የተለያዩ መሆናቸውን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡ አሜሪካዊያን ተናገሩ፡፡
ከአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት የመጡት ሬይ ማክልስ እንደገለጹት፣ በምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የምትሰማውና ቦታው ላይ ተገኝተህ የምታየው ነገር መሬት ላይ ካለው እውነት ይልቅ የሚዲያው ውሸት ይገዝፋል ብለዋል።
እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ተዘዋውረን ባየናቸው አከባቢዎች ምንም የገጠመን ችግር የለም ያሉት ሬይ የምዕራቡ ሚዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ግጭት እንዳለና ሀገሪቷ ያልተረጋጋች አድርገው የሚያሰራጩት ዘገባ ተገቢነት የለውም፤ ለምን እንደሚዘግቡም ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ላለፉት 20 ዓመታት ለመጎብኘት የተመላለሱት ሌላው አሜሪካዊ ፖል አንደርሰን በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያ ስለኢትዮጵያ የሚያሰራጫቸው መረጃዎች ከእውነት የራቀ ነው ሲል ተናግረዋል፡፡
ከአንድ ሬስቶራንት ቁጭ ብዬ የሲኤንኤን ዘገባ ስመለከት በጣም አስቂኝ ነው የሆነብኝ፤ ምክንያቱም ሚዲያው በወቅቱ እያሰራጨ የነበረው መረጃ ኢትዮጵያ በግጭት ማዕበል እየተናጠች ነው ይላል፤ ይህም የት ብለህ እንድትጠይቅ ያደርግሃል ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደኢፕድ ዘገባ ኢትዮጵያ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ ያካሄደችውን ምርጫ አዲስ አበባ ከተማ በመገኘት የምርጫውን ሂደት የማየት እድል እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡