መስከረም 13/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ምርመራ መርህን ከሚያከብሩ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥል በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ተናገሩ።
የአሸባሪው ህወሓትን የፖለቲካ መግለጫ የሰብዓዊ ምርምራ ሪፖርት አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረግ ጥረትን ኢትዮጵያ በፅኑ የምታወግዘውና የማትቀበለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ አካሂጄዋለሁ ያለውን የሰብዓዊ መብት ምርምራ ሪፖርት ላይ ትናንት ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ሪፖርቱ ከደረጃ በታች የሆነ፣ ሙያዊ ይዘት የጎደለውና ግድ የለሽነት የተሞላበት በመሆኑ እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።
አምባሳደር ዘነበ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የምርመራ ተቋማት ጋር መርህን በጠበቀ መልኩ ስትሰራ መቆየቷን ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር ማድረጓን በመጥቀስ።