ኢትዮጵያ ዘመናዊና ፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንባት መቻሏን ተረድተናል – የሞሮኮ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

ሐምሌ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ዘመናዊና ፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንባት መቻሏን መረዳታቸውን የሞሮኮ ምክትል ኢታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል አዚዝ እድሪስ ገለጹ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ በሞሮኮ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል አዚዝ ኢድሪሲ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሜጄር ጄኔራል አዚዝ ኢድሪሲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የመከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን እንደጎበኙ ጠቁመዋል።

በመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ባደረጉት ጉብኝት ሰፊ ልምድ መቅሰማቸውንና በቆይታቸው ለተደረገላቸው መልካም አቀባባል ምስጋና አቅርበዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው በሞሮኮና በኢትዮጵያ መካካል ያለው ግንኙነት ታሪካዊና የቆየ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ጉብኝትም ይህንን ግንኙነት በወታደራዊ እና በሌሎች መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ቦታ እንዳለው መናገራቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡