ኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይ የሁልጊዜ አጀንዳዋ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ

ኅዳር 2/2014 (ዋልታ)  የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ በርካታ ዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ዘመቻ ቢያካሂዱም ያሰቡትን ማሳካት እንዳልቻሉ ተነገረ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው ኢትዮጵያን በተመለከተ ተቀነባብረው የሚቀርቡ በርከት ያሉ የሀሰት መረጃ ዘመቻዎችን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በትኩረት በመስራት እቅዳቸውን እና ዓላማቸውን ማክሸፍ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይ የሁልጊዜ አጀንዳዋ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና በመንግሥት በኩል ያለው እና የነበረው ፍላጎት ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተም ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች ማብራሪያ መሰጠቱን በመግለጫቸው አንስተዋል።

ከተለያዩ አገራት ተወካዮች እና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ውጤታማ  ውይይቶች መደረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡