ኢትዮጵያ የሰው ሃብትን ተጠቅማ ምጣኔ ሃብቷን ታበለጽጋለች ተባለ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የሰው ሃብትን ተጠቅማ ምጣኔ ሃብቷን ማበልፀግ እንደምትችል ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በዓለም ባንክ ትብብር የተዘጋጀው የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች አገራዊ የስልጠና መርኃ-ግብር ተጀምሯል።

በኢትዮጵያ ብቸኛው የፖሊሲ ባንክ በመሆን ላለፉት 114 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ልማት ባንክ ኢትዮጵያን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር በርካታ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል።

የተለያዩ አገራት አምራቹን ወጣት ሀይል ተጠቅመው በመስራታቸው ኢኮኖሚያቸውን ከማሳደግ ባለፈ የማይናወጥ አቅም ያላቸው ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር መቻላቸው ይነሳል።

በማደግ ላይ ካሉ አገራት ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት መበልፀግ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር፣ በስልጠና ብሎም አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በማብቃት ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዩሀንስ አያሌው ከለውጡ በፊት ያሉበትን የሥራ ግድፈቶች አርሞ ወደ ሥራ የገባ ተቋም መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ ተቋሙ በአዲስ አመራር የአገርን ኢኮኖሚ ለማጎልበት እየሰራ እንዳለ ጠቁመዋል።

በመላው አገሪቱ ለሦስተኛ ጊዜ የሚሰጠው ስልጠና ከ34 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰልጣኖች በ20 ከተሞች በተዘጋጁ የስልጠና ማዕከላት እንደሚሰለጥኑ ተገልጿል።

ከልማት ባንክ ጋር በመተባበር ወጣቱ የሙያ እና የሊዝ ፋይናንስ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

ባንኩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ የሚገቡበትን 14 ቢሊየን ብድር ማጽደቁን አስታውቋል።

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመስሪያ ቦታን ከማቅረብ ጀምሮ እንደየክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።

በሀኒ አበበ