ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ሰላማዊ ዜጎች የአየር ኃይል ጥቃት ሰለባ አልሆኑም አሉ

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

ጥር 14/2014 (ዋልታ) አየር ኃይላችን የታጠቀው መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

አሸባሪው ሕወሓት “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” ሲል የሚያቀርበውን ውንጀላ ከእውነት የራቀ ብለውታል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ይህም አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የኅልውና አደጋ በብቃት በመመከት ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲያበረክት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።

አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ከየትኛውም ወገን የሚቃጣን ጥቃት ለመመከትና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተደራጀ ነው ያሉት ዋና አዛዡ ‘የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ የተሰጠውን ዒላማ በብቃት የሚመታ በመሆኑ በምንም መልኩ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም’ ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የአሸባሪው ሕወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል “በትግራይ ክልል በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” በሚል የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን አብራርተዋል።

አየር ኃይሉ ሕዝባዊ መሰረት ያለውና በጠንካራ ሥነ ምግባር የተገነባ በመሆኑ የትኛውም አይነት ኦፕሬሽኖች ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

የአየር ኃይሉ ዘመናዊ ትጥቆች ማንን እና ምን መምታት እንዳለብን በዓይናችን አይተን እንድንወስን የሚያደርጉ በመሆናቸው በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈጸም አይችልም ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ህጻናትን የያዙ እናቶችን ጭምር አስገድዶ በጦር ካምፕ ውስጥ በማስገባትና የጥቃት ዒላማ እንደሆኑ አስመስሎ ፊልም በመቅረጽ እንደሚያሰራጭ ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችም የራሳቸው የሆነ መለዮ የሌላቸው በመሆኑ የቡድኑ አመራሮች በጦርነቱ የሞቱባቸውን ታጣቂዎች አስከሬን በመሰብሰብ ሠላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ አስመስለው ዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየጣሩ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

የአየር ኃይሉ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያን በሚመጥንና ኢትዮጵያዊያንን በሚመስል መልኩ የተገነባ እንዳልነበረ፤ በአንድ አካባቢ ሰዎች ታጥሮ ለአንድ ፓርቲ ኅልውና ሲሰራ እንደቆየም አንስተዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ለታላቅ አገር የሚመጥንና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሆነ ተቋም መገንባት መቻሉንም ነው የገለጹት።

ይህን ተከትሎ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ወጣቶች ተቋሙን በመቀላቀል ስልጠና እየወሰዱ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል።

የአየር ኃይሉ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ከደኅንነት ስጋት ነጻ እንዲሆን በመጠበቅ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለምንም ችግር የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ተቋሙን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ይበልጥ ለማዘመን አዳዲስ አሰራሮች ወደ ትግበራ እንደሚገቡም አንስተዋል።