ጥቅምት 20/2014 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በአሸባሪው ሕወሓትና አጋሮቹ ያልተቋረጠ ጥቃት፤ በምእራባውያንና ተቋሞቻቸው ደግሞ በታሪክ የማይረሳ ክህደትን እያስተናገደች መሆኑን እንግሊዛዊው ጸሃፊ ግራሃም ፒብልስ ካውንተርፓንች ለተባለው ድረገጽ በላኩት ሰፋ ያለ ጽሁፍ ገለጹ።
አሸባሪው ሕወሓት የሚያደርሳቸውን ግፍና ሰቆቃዎች ችላ በማለት ለቡድኑ ጥፋቶች ይሁንታን እየሰጡ ያሉት ምእራባውያንና ያሰማሯቸው የሚዲያ አካላት ኢትዮጵያውያን ላደረጉት ብሄራዊ ምርጫና ለመሰረቱት መንግስት እውቅና ከመስጠት ተቆጥበዋል ብለዋል።
ጸሃፊው ድርጅቶቹና ሃላፊዎቻቸው አሁንም በተቀናጀ መንገድ ስም ማጥፋት ላይ በርትተው እየሰሩ ሲሆን አልጀዚራ፤፣ ኔውዮርክ ታይምስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ቢቢሲ እንዲሁም ፌስቡክን የመሳሰሉ ተቋማትም በርትተው ኢትዮጵያን እያጠለሹ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ እርዳታ አግዷል፤ የዘር ማጽዳት ፈጽሟል የሚሉ የስም ማጥፋት ዘመቻዎቻቸው መጀመሪያና መጨረሻ ከሆኑ ሰነባብተዋል የሚሉት ጸሃፊው ከመሰረታዊ የጋዜጠኝነት መርሆች በራቀ ሁኔታ ክሶቹን የሚያዘጋጁት አፍቃሬ አሸባሪው ሕወሓት ከሆኑ ምሁራን ተብዬዎችና ከድርጅቱ አባላት ብቻ መሆኑ ዘገባዎቹ እውነተኛና ሚዛናዊ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ጸሃፊው የኢትዮጵያ መንግስትን በርትተው የሚወነጅሉት እነዚሁ የሚዲያ ተቋማተና የምእራባውያኑ ባለስልጣናት አሸባሪው ህወሃት በአማራና በአፋር ክልል ንጹሃን ዜጎችና እንስሳት ላይ ያደረሳቸው ግፎች ምንም ስሜት ሊሰጣቸው ያልቻለው ቡድኑ እ.ኤ.አ ከ1991 እስከ 2018 ድረስ በታማኝነት ሲያገለግላቸው በመቆየቱ ስራውን እንዳያቆም ፍላጎት ስላላቸው መሆኑን ገልጿል።
አሸባሪው ሕወሓት ስልጣን ላይ እያለ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰውን መከራ ሊመለከቱ ያልፈለጉትም በዚህ ምክንያት ነው ማለታቸውን የኢዜአ መረጃ አመላክቷል፡፡
አሸባሪው ቡድን በአለም አቀፍና በታላላቅ ድርጅቶች ውስጥ የሰገሰጋቸው ግለሰቦችና በገንዘብ አፋቸውን ያስያዛቸው ባለስልጣናት ሊነገሩ የማይችሉ ግፎች በአሸባሪው ሲፈጸሙ ትንፍሽ አለማለታቸው ሊደንቅ አይገባም ብለዋል።
የድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከተቀበሉት አለም አቀፍ ሃላፊነት በተጻረረ መልኩ ጊዜና ትኩረታቸውን በሕወሓት ስራ ላይ በማዋል የተመ ሃላፊዎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው እንዲዳክሩ በማድረግ የድርጅቱን ገለልተኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደከተቱትም አስረድተዋል።
ጸሃፊው የተመድ ሃላፊዎች ከኢትዮጵያ መባረርን ተከትሎ ራሳቸውን አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሉት ምእራባውያን ቁጣቸውን በመግለጽ የማእቀብ ማስፈራሪያዎችን ቢያቀርቡም እስካሁን የተተቀየረ ነገር አለመኖሩን አንስተው፤ ኢትዮጵያውያን የምእራባውያኑን ትእዛዝ ባለመቀበል በአቋማቸው የጸኑት ጠንካራ የነጻነትና የአልገዛም ባይነት መንፈስ ባለቤቶች ስለሆኑ ነው ብለዋል።
አፍቃሬ ሕወሓት የሆኑት ምእራባውያን እውነታዎችን በማዛባት ለአሸባሪው ድርጅት የሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ችግሩን በማባባስ ንጹሃንን ሰለባ በማድረግ የብዙዎችን ህይወትና ንብረት በማጥፋት ላይ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን ላይም የህሊና ጠባሳ ከመፍጠር ውጭ የምእራባውያኑን ፍላጎት እውን እንደማያደርግ ሊታወቅ እንደሚገባም አስታውሰዋል።
ምእራባውያኑ የፈለጉትን ቢሉም አፍሪካውያን ወንድሞቻቸውን የክብር እንግዶች በማድረግ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ምርጫ መንግስታቸውን በአዲስ ምእራፍ መመስረት እንደቻሉ፤ ለአለም አሳይተዋል ያሉት ጸሃፊው በወቅቱም አፍሪካውያን ለቅኝ ገዥዎቻቸው መላላክ ማቆማቸውን ያሳዩበት ሆኖ ማለፉን አብራርተዋል።