ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ውድድር አሸናፊ ሆነች

ሚያዝያ 3/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ውድድር አሸናፊ ሆነች።
ለሁለት ቀናት በራስ ኃይሉ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ሲካሄድ የነበረው ሻምፒዮና ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች በ24 ወርቅ፣ በ23 ብርና በ33 ነሐስ በድምሩ 80 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች።
ሜዳሊያዎቹ የተገኙት በቴኳንዶ ትዕይንት (ፓተርን)፣ ፍልሚያ (ስፓሪንግ) እና ‘ፖወር ቴስት’ በተሰኙ የውድድር አይነቶች ነው ተብሏል።
ሴኔጋል በአንድ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ሞዛምፒክ በሁለት የብር ሜዳሊያ ሦስተኛ ወጥታለች።
በወንዶች በእምነት ሹሜና አቤነዘር መኮንን እንዲሁም በሴቶች ዳግም ኪሮስና ሀና አበባየሁ የሻምፒዮናው ኮከብ ተጫዋች ሽልማት (ጎልደን ግሎቭ) አግኝተዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ፣ ጋምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛንያ፣ ኮትዲቭዋር፣ ሞዛምቢክ፣ ጅቡቲ፣ ብሩንዲና ዚምባቡዌ ተሳታፊ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።