“ኢትዮጵያ የወታደሮች ላብ፣ ደም እና አጥንት ያፀናት ታላቅ ሀገር ናት!” – የገንዘብ ሚኒስቴር

ነሐሴ 26/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የወታደሮች ላብ፣ ደም እና አጥንት ያፀናት ታላቅ ሀገር ናት ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

“ኢትዮጵያ የወታደሮች ላብ፣ ደም እና አጥንት ያፀናት ታላቅ ሀገር ናት!”

አፈር ገፍተው፣ አረም ጎልጉለው የሚያበሏት ባለ እርፍ ወታደሮች ሀገር ናት። መንገዷን በእውቀት ብርሃን የሚተልሙላት የባለአዕምሮ ወታደሮችም ሀገር ናት ሃብት የሚያፈሩላት፣ የሚመጥኑላት፣ የሚያከፋፍሉላት ባለ ላብ ወታደሮች ሀገር ናት። ሁላችንም የኢትዮጵያ ወታደሮች ነን፤ ሁላችሁም የኢትዮጵያ ወታደሮች ናችሁ። ጥቃት የማንሸከም፣ ዳሯ መሃሏ በክብር እና በሰላም እንዲያድር የምንዋደቅ ወታደሮቿ ስጋችን ፈርሶ፣ ደማችን ፈሶ፣ አጥንታችን ተከስክሶ በታላቅ ሀገርነት ኢትዮጵያን እናፀናታለን።

የኢትዮጵያ በመሆናችን ሁሌ እንኮራለን። በደስታ እና በክብር እንጠብቃታለን። በደስታ እና በክብር እንሰዋላታለን ዛሬ ኢትዮጵያ ተበታትና፣ ተዳክማ፣ እንድትወድቅ እና እንድትፈርስ የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቿ ከውስጥ አሸባሪ ቡድኖች ጋር በመተባበር ጥቃት ከፍተውባት በጽኑ መከላከል ላይ ትገኛለች።

በተለያየ ዙር ጠላቶቿ ልጆቿን ደፍረው-አጎሳቁለው-ገድለው፣ ንብረታቸውን አጥፍተው፣ መማሪያ-መታከሚያ-መኖሪያ-ማደሪያ-ማምለኪያ-ፈጣሪን መለማመኛቸውን አውድመው ማጥቃታቸው መራር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ጀግኖች ልጆቿ በተለያዩ ጊዜያት የተሰነዘሩ ጥቃቶችን በጽኑ መክተው፣ መስዋዕት ሆነው አኩሪ ምላሽ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያን አስቀጥለዋል። በዚህ ሁሉ የፈተና እና የድል ጉዞ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ እና ድጋፍ ድንቅ ነበር።

የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በጽናት ተከላክላችኋል፤ በዐበይቶቹ የአለም መዲናዎች ዝናብ፣ ብርድ እና ቁር፣ሙቀትና ሃሩር ሳይበግራችሁ ለኢትዮጵያ ተሰልፋችሁ ስለኢትዮጵያ ድምፃችሁን አስምታችኋል፧ በየሃያላኑ ደጅ ስለኢትዮጵያ ባክናችኋል-ተንከራታችኋል፧ ገንዘባችሁን፣ እውቀታችሁን፣ ደማችሁን… ለግሳችኋል: አስተባብራችኋል፤ ተባብራችኋል። ታሪክ ይኼን በደማቁ ፅፎታል።

ዛሬ የኢትዮጵያ የፈተና እና የድል ጉዞ ወሳኝ መታጠፊያ ላይ ደርሷል። የኢትዮጵያ ጠላቶች በሀገራችሁ እና በሰላም ወዳዱ ወገናችሁ ላይ ዳግም ጥቃት አውጀዋል የተጠናወታቸውን እኩይ ኢትዮጵያን የማዋረድ ተግባር እንደገና ጀምረዋል።

ይህንን የተቃጣብንን ጥፋት ጀግኖቹ የኢትዮጵያ መከላhያ ኃይሎች ከሰላም ወዳዱ ደጀን ህዝባችን ጋር በመሆን በጽናት እና በጀግንነት እየመከቱ ይገኛሉ። ይህ ተዋድቋችን ለሀገራችን የሚሰነብት፣ የሚከርም፣ ለረዥም ጊዜ ፀንቶ ሊኖር የሚችል ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት ነው።

በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያንም እንደተለመደው ለዚህ ትግል እያደረጋችሁት ያለውን ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን። አካላችሁ ከሃገራችሁ ቢርቅም ልባችሁና ሃሳባችሁ ከኢትዮጵያ ጋር ነውና ባላችሁ አቅም ኢትዮጵያን ለማገዝ እንዲያስችላችሁ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንቶች ተዘጋጅተዋል።

  • Euro- 1000439142832 (ዩሮ)
  • Usd 1000439142786 (ዶላር)
  • Gbp- 1000443606304 (ፓውንድ)

ሁላችንም፤ ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ታላቁን ሰማዕት ብፁዕ አቡነ

ጴጥሮስን በተውኔቱ እንዳናገራቸው:

“..ጽናት ስጪኝ እንድካፈል የኢትዮጵያን ዕዳ፣

ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ ከነደደችበት እቶን፣

የሷን ሞት እኔ እንድሞታት ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፣” የምንልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።

ለምትወዷት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን የማፅናት ትግል በየቆማችሁበት ጽኑ እና ንቁ ወታደሮቿ የምትሆኑበት ጊዜ አሁን ነው!

ለታላቋ ኢትዮጵያ ክብር በጽናት እናብር።

ልጆቿ ይህን ወሳኝ ጊዜ በወሳኝ ታሪካዊ ድል እንወጣዋለን፡

ኢትዮጵያ ምንጊዜም ታሸንፋለች