ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለመጠቀም የማንም ቡራኬ የምትጠይቅ አለመሆኗን ለዓለም ለማሳወቅ የዲፕሎማሲው ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ።
የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን ለመጠቀም የማንም ቡራኬ የማትጠብቅ መሆኗን ለዓለም ግንዛቤ ለማስጨበጥ የዲፕሎማሲው ሥራ መጠናከር እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን እውነታ ዓለም እንዲገነዘበው የመገናኛ ብዙኃን የራሳቸውን ሚና መወጣት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ፣ የሕግና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት በአባይ ላይ ባላቸው የተንሸዋረረ አመለካከት ኢትዮጵያ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንዲሁም ከአባይ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷ ተነግሯል።
በዓለም ላይ ያሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለመቀየር ፐብሊክ ዲፕሎማሲን ማጠናከር እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የሕዳሴ ግድብ ሙሉለሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በተፋሰሱ አባል ሀገራት የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለመኖሩን ለሀገራቱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የዲፕሎማሲው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተነስቷል።
ዙፋን አምባቸው (ከአርባምንጭ)
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW