ኢትዮ ቴሌኮም “ኮንታክት ሴንተር” የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አደረገ

ጥቅምት 8/2015 (ዋልታ) ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ “ኮንታክት ሴንተር” የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡

አገልግሎቱ ኢንተርፕራይዞች በቀላሉ ከደንበኞቹ ጋር የሚገናኙበት፣ ምርት እና አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡበት ሲሆን ተገልጋዮች መደበኛ የስልክ ኔትዎርክን ጨምሮ ሁሉንም የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ሁሉ በመጠቀም የሚፈልጉትን አገልግሎት በቀላሉ የሚያገኙበት ነው።

ቴክኖሎጂው ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጥ ከነበረው የጥሪ ማዕከል የተቀላጠፈና ዘመናዊ ነው ተብሎለታል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍረህይት  ታምሩ  እንደገለፁት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከሚያስችሉ አማራጮች ውስጥ አንዱ ይሆናል የተባለው ይህ ኮንታክት ሴንተር የኢትዮ ቴለኮምን ተደራሽነት ከፍ ከማድረጉም ባሻገር የኩባንያውን ኢንተርፕራይዞች አቅም የሚያሳድግ ነው።

ከዚህ ቀደም የነበረው የጥሪ ማእከል አሰራር አገልግሎቱን ውስን እንዲሆን አድርጎት እንደነበርም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡

ምክንያቱም የጥሪ ማዕከል አገልግሎት በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ብቻ የተመሰረተ ከመሆኑም ባሻገር የድምፅ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው።

ነገር ግን ይህ አገልግሎት ካለምንም የገመድ ዝርጋታ የሚከናወን የአገልግሎት አሰጣጥ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ኩባንያዎች የጥሪ ማዕከላት ቅሬታን ብቻ የሚያስተናግዱበት የነበረ ሲሆን ይህ አገልግሎት ግን መደበኛ የስልክ መስመርን ጨምሮ ሁሉንም ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያስጠቅሙ ድረገፆችን እንዲሁም እንደ ቴሌ ብር ያሉ የገንዘብ ማንቀሳቀሻ አማራጮን በማካተት ኩባንያዎች ምርት እና አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡበት ነው።

ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተነገረለት ኮንታክት ሴንተር ቀልጣፋ እና ወጪና ሰዓት ቆጣቢ አገልግሎት ነውም ተብሏል።

የአገልግሎት አሰጣጡም በርካታ የኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን በራሱ እየቀያየረ ደንበኞች የሚስተናገዱበት፤ ምርቶች በኦን ላይን የሚገበያዩበት እና ደንበኞች ከወኪሎች ጋር ሳይገናኙ ራሳቸውን የሚያስተናግዱበት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

ኢትዮቴሌኮም ወደ 68 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉትም ተገልጿል፡፡

በሚልኪያስ አዱኛ