ኢትዮ-ቴሌኮም የዲጂታል ትምህርት ማዕከላትን አስመረቀ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) ኢትዮ-ቴሌኮም በ66 የፌደራል እና የክልል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያቋቋመውን የዲጅታል ማዕከላት አስመርቋል::

ኢትዮ-ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በያዘው እቅድ መሰረት ያቋቋማቸው እነዚህ ማዕከላት፤ ኮምፒውተሮች፣ ልዩ ልዩ የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎችን እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት የተሟላላቸው ናቸው፡

ከእነዚህ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 18ቱ በአዲስ አበባ፣ ቀሪዎቹ 48 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በክልሎች የሚገኙ ሲሆን የተጠቃሚ ትምህርት ቤቶቹ የተመረጡት የአዲስ አበባ እና ክልል ትምህርት ቢሮዎች ከኢትዮ-ቴሌኮም የሪጅንና የዞን ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዲጂታል ማዕከላቱ 140 ሺሕ ገደማ ተማሪዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ ሲሆን የትምህርት ስርዓቱን አንድ ደረጃ ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል::

የዲጂታል መማሪያ ማዕከሎቹ መገንባት የቴክኖሎጂና አዲስ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር፣ ተማሪዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂው ጋር አብረው እንዲጓዙ ለመደገፍ፣ የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ የበጎ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ተሳትፎ በትምህርትና ሥልጠና በማጎልበት እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ለሚኖሩበት ማህበረሰብ እንዲያካፍሉ እንደሚያግዝ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል:

በተጨማሪም ሙያዊ ትንታኔ እና ችግር ፈቺ ክህሎቶችን ለማዳበር ለትምህርት ቤቶች እና ለተማሪዎቻቸው ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

በሔብሮን ዋልታው