ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት በጎንደር ከተማ አስጀመረ

ሃምሌ 03/2013 (ዋልታ) – ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጂን የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት በጎንደር ከተማ አስጀምሯል።

አገልግሎቱ ከጎንደር ከተማ በተጨማሪ በደብረታቦር ያሉ ደንበኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሒወት ታምሩ በአሁኑ ወቅት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች በኢንተርኔት ላይ የተመረኮዙ በመሆናቸው ኢትዮ ቴሌኮምም ይህንን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማፋጠን በ67 ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን ገልፀዋል።

አክለውም  በሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጂን 142 ሺህ ዜጎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀው 72 ሺህ የሚሆኑት ዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ በመሆናቸው የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት በተጨማሪ የገንዘብ ልውውጥና ክፍያዎችን ማዘመን የሚችለውን ቴሌ ብር አገልግሎቱን ይፋ አድርጓል።

ይህ አገልግሎት የኢንተርኔት ግብይት አገልግሎትን  ይበልጥ እንደሚያፋጥነውም ተነግሯል።

(በዙፋን አምባቸው)