ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ ኤል ቲ ኢ የኢንተርኔት አገልግሎት በሀረር፣ አወዳይ እና ሀረማያ ከተሞች አስጀመረ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስ የኢንተርኔት አገልግሎት በማእከላዊ ምስራቅ ሪጅን በሀረር፣ አወዳይ እና ሀረማያ ከተሞች በይፋ አስጀምሯል።

በመርኃግብሩ የደምበኞች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ትውውቅ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

ተቋሙ በዲጅታል ኢኮኖሚ ተቋማትን ለመቃኘት ብሎም የግብይት ስርዓቱን ለማዘመን መሰረተ ልማት በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።

በተያዘው በጀት አመት በ103 ከተሞች የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስ ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁሟል።

በማዕከላዊ ምስራቅ ሪጅን በ33 ከተሞች 67 ሺህ ተገልጋዮች ማግኘት እንደሚችሉ የኢትዮ የቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።

የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስ አገልግሎት ምስሎችን በፍጥነት ለማውረድ እና መለዋወጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

አዲሱ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ገንዘብን በእጅ ስልኮች ማንቀሳቀስ የሚያስችል የቴሌ ብርን ማስተዋወቁ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአምስት አመት ውስጥ 3.5 ትሪሊዮን ብሮችን በቴሌ ብር ለማንቀሳቀስ መታቀዱንና በሁለት ሳምንት ውስጥ 2.4 ሚሊየን ተገልጋዮች የቴሌ ብር ቤተሰብ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

(በሃኒ አበበ)