ኢንስቲትዩቱ ለመልሶ ማቋቋሚያ ከ5.1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

የካቲት 24/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ኢንስቲትዩቱ ካደረገው ድጋፍ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን 120 ሺሕ ብር ግምት ያለው ደግሞ የቁሳቁስ ድጋፍ መሆኑ ታውቋል።

ድጋፉን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።

ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም ተመሣሣይ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ወገኖቻችንን ለማገዝ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ ኢንስቲትዩቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎችም ተመሳሳይ ድግፍ በማድረግ ለወገን ደራሽ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW