ኢንስቲትዩቱ ተጠባቂውን የግንቦት ወር ዝናብ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳሰበ

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) በአገሪቱ አብዛኛው አካባቢዎች የሚጠበቀውን የግንቦት ወር ዝናብ በአግባቡ ለመጠቀምና ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ እንደገለጸው የግንቦት ወር ዝናብ ሰጪ የሜትሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የአገሪቱ ሥፍራዎች ላይ አንጻራዊ ጥንካሬያቸውን ይዘው እንደሚቀጥሉ የትንበያ መረጃዎቹን ይጠቁማሉ ብሏል።

ይህንንም ተከትሎ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚኖር ትንበያ አስቀምጧል።

በደቡብ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦችና በጋምቤላ አካባቢ ጥቂት ሥፍራዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ የማስከተል አቅም ያለው ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል።

በግንቦት ወር ከምስራቅ ሃረርጌ ምስራቅ ዞኖች በስተቀር በሁሉም የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ላይ፣ በቤንሼንጉል፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ክልል፣ በሲዳማ ክልል በሁሉም ዞኖች እንዲሁም በአማራ ክልል በአዊ፣ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች ላይ ከመደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል።

አልፎ አልፎ ከሚፈጠሩ የደመና ክምችቶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃው ያመለክተል።

በተጨማሪ በጎንደር ሁሉም ዞኖች በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ ከአፋር ክልል፣ በምስራቅ ሀረርጌ፣ በምስራቅ ባሌ፣ ከሱማሌ ክልል በዳዋ፣ በሊበንና አፍዴራ ዞኖች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል።

በተቀሩት የአገሪቱ አከባቢዎች ደረቃማ ሆነው እንደሚሰነብቱ የአየር ትንበያው መረጃ አመላክቷል።

ከቀላል እስከ ከባድ የሚጠበቀው የዝናብ መጠን በአብኛዛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለረጅም ጊዜ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት መሻሻል ትልቅ እድል እድል እንደሚፈጥ ተገልጿል፡፡

የሚገኘውን ውኃ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የተለያዩ የውኃ ማቆያ ዘዴዎችን በመጠቀም ዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚያጋጥማቸውን የእርጥበት እጥረት ለማቃለል እንደሚረዳ ተገልጿል።

ከባድ ዝናብ በሚከሰትባቸው የአገሪቱ አከባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያጋጥም ስለሚችል ሰብሎች እንዳይጎዱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በተጨማሪም ከእርጥበት መብዛት ጋር የጸረ-ሰብል ተባይና የአረም መከሰት ሊኖር ስለሚችል ለዚህም ጥንቃቀቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ከክረምት እርጥበት መጠናከር ጋር ተያይዞ በደቡብ ምዕራብና በምዕራቡ የአገሪቱ የውኃ አካሎች ላይ የእርጥበት መጠኑ እንደሚጨምርም የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

ይህንንም የእርጥበት መጠን ጥቅም ላይ ለማዋልና የሚያስከትለውን አሉታዊ ጎን ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቲ ገልጿል፡፡