ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ኢንቨስተሮች፣ ባለሀብቶች እና የንግድ ማህበረሰብ በጉለሌ እፅዋት ማእከል በመገኘት የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡
በፕሮግራሙ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ አሁን እያካሄድነው ያለው የኢትዮጵያን እናልብስ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ በተሻገረችበት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ባካሄደችበት ማግስት መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለምግብነት የሚሆኑ ችግኞች እንደሚተከሉም ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት አማካሪ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ ሀገር ለመገንባትና ሥርአት ለመገንባት ሀሩሩን፣ ዝናቡን እንዲሁም ረሃቡን ተቋቁሞ የሀገር ፍቅሩን በሰላማዊ ምርጫ አሳይቷልና ክብር ይገባዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ቡዙ የጎደሏት ነገሮች አሉ፤ እኛ እንድንሞላው ይጠበቃል ያሉት ዶክተር አለሙ፣ ችግኝ ከመትከል ባሻገር አንድነታችንን በማጠናከር የሀገር ግንባታውን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈርሃት ካሚል እንደሀገር ለጀመርነው የእድገትና ዴሞክራሲን የመትከል ጅምር ችግኝ መትከሉ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ችግኝ መትከል ባህል ወደ ማድረግ ተሸጋግረናል ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም አክለዋል ።
በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደ ሀገር 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ደረጃም ከ7 ሚሊየን በላይ ችግኞች ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
(በሳራ ስዩም)