ኢዜአ 5 ሺሕ መጻሕፍት ለአብርሆት አበረከተ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከ5 ሺሕ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ።
“አንድ ሚሊየን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የተለያዩ ተቋማትና አካላት መጻሕፍት በመለገስ ላይ ይገኛሉ።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሰራተኞቹ ያሰባሰበውን ከ5 ሺሕ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አበርክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ትውልድ የሚቀረፅበት ትልቅ ስፍራ በመሆኑ በ38 የኢዜአ ቅርንጫፎች ከሚሰሩ የድርጅቱ ሰራተኞች ያሰባሰበውን ከ5 ሺሕ በላይ መጻሕፍት አበርክቷል ብለዋል።
ይህ ጅምር እንጂ መደምደምያ አይደለም ያሉት ኃላፊው በቀጣይም መጻሕፍት በማሰባሰብ እንደሚያበረክቱም ተናግረዋል።
ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት በከፍተኛ ተነሳሽነት የተለያዩ ተቋማትና አካላት መጻሕፍት እየለገሱ መሆኑን የገለጹት የቤተ-መጻሕፍቱ ኃላፊ መስፍን ገዘሀኝ አሁንም መጻሕፍትን በማበርከት ለትውልድ የሚያልፍ አሻራን ማስቀመጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በርክክቡ ወቅት የተገኘው አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ መጻሕፍት የሳሎን ማጌጫ መሆን እንደሌለባቸውና ወደ ሳጥን ገብተውም ለአይጥ ራት ከሚሆኑ ይልቅ ትውልድ እንዲማርበትና እንዲቀየርበት መደረግ አለበት ብለዋል።
በታምራት ደለሊ