ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የጥንቃቄ ስራዎችን በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰርን ተከትሎ በተከሰተው ተቃውሞና አመጽ በዙሉ ናታልና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን መጋናኛ ብዙኋ እየዘገቡ ይገኛል።
በአንዳንድ አካባቢዎችም በኢትዮጵያውያን የንግድ መደብሮች ላይ ጉዳት መድረሱን ኢዜአ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ዜጎች ያገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባሉት አደረጃጀቶች መግለጫ ሰጥቷል።
ኤምባሲው “ኢትዮጵያውያን ችግሩ ካሉባቸው ቦታዎች እንዲርቁና የንግድ መደብሮቻቸውን በመዝጋት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስታውቋል” ብለዋል።
“ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅትም ለኤምባሲው የሚያሳውቁበት አድረሻ ለዜጎች ተሰጥቷል ያሉት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያውያኑ ተሰባስበው እርስ በእርሳቸው መረጃ እንዲለዋወጡም ተደርጓል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ኤምባሲው ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቁመው የደረሱ ጉዳቶች ካሉ በማጣራት መንግስት እንደሚሰራና አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃክ ኦፍ ዙማ በተጠረጠሩበት የሙስና ክስ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆናቸው አረጋግጦ የ15 ወራት እስር እንደፈረደባቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው ሰሞኑን ባስነሱት ከፍተኛ አመጽ 30 ሰዎች መሞታቸው ሲገለጽ በጥቃቱ የተሳተፉ በ 800 ሰዎች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።