‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ በሜሪላንድ ግዛት ተካሄደ

‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የተሳተፉበት ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ሴክዩሪቲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በሜሪላንድ ግዛት ተካሄደ።

ሰልፉ የኮንግረስ የዴሞክራት ፓርቲ መሪ ስቴኒ ሆየር (ሜሪላንድ) ቢሮ ፊት ለፊት የተካሄደ ሲሆን በሰልፉ ላይ በሜሪላንድ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የግዛቱ የኮንግረስ አመራር ሕጉን ለሕግ አውጪው አካል እንዳያቀርቡት ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማኅበር የዋሺንግተን ግብረ ኃይል ያገኘው መረጃ አመላክቷል።

‘ኤችአር 6600’ ኢትዮጵያንና ኤርትራን እንዲሁም የኢትዮጵያና የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚጎዳ በመሆኑ መሰረዝ አለበት የሚሉ መልዕክቶች መተላለፋቸው ተገልጿል።

የሰልፋ አስተባባሪዎች ስለ ረቂቅ ሕጉ ጎጂነት የሚያስረዳና ሕጉ ለኮንግረስ እንዳይቀርብ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለስቴኒ ሆየር ቢሮ አስገብተዋል።

ከሰልፉ በተጨማሪ የኮንግረስ የዴሞክራት ፓርቲ መሪ ስቴኒ ሆየር ጋር በበይነ መረብ ውይይት ለማድረግ ለነገ ቀጠሮ መያዙን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።

ውይይቱ በሜሪላንድ ግዛት የሚኖሩ ብዙ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ለኮንግረሱ አመራር ረቂቅ ሕጉን እንደሚቃወሙት ለማሳወቅና በሕጉ ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክቷል።

የዳያስፖራ ተቋማትና አደረጃጀቶች የኮንግረስ አባላትንና ሴናተሮችን በማነጋጋር፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ፣ ደብዳቤ በመጻፍና የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ዘመቻ በማድረግ ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ አስፈላጊውን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ጎጂ የሆኑት ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ድምጻቸውን ማሰማት እንዲቀጥሉ ነው ግብረ ኃይሉ ጥሪ ያቀረበው።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

‘የኤችአር 6600’ አጋዥ (ኮምፓኒየን) የሆነው ‘ኢትዮጵያን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕግ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣ በሴናተር ጀምስ ሪስች (ኢዳሆ)፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ (ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ (ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ሲሆን ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት መወሰኑ ይታወሳል።