ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ አድርጎ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – የኤች አይ ቪ/ኤድስ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይበልጥ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
ጽህፈት ቤቱ የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅዱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የጽ/ቤቱ ዋና ኃላፊዋ ዶ/ር ፅጌሬዳ ክፍሉ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የኤች አይ ቪ ስርጭት ከፍተኛ የሆነባቸው 265 ወረዳዎች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሥራዎችንም ይበልጥ ተጋላጭና ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በለየና ታሳቢ ባደረገ መንገድ መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡
በወረዳዎቹም የተለየ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኢፕድ ዘገባ እንዳመለከተው በከፍተኛ ርብርብና ልፋት የተዘጋጀው ሀገራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ ስትራቴጂክ እቅድ (2014-2018 ዓ.ም) በመርሃ-ግብሩ መሰረት እንዲተገበር የሁሉንም አካላት የተጋ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና የክልል የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ኤችአይቪ መከላከያ ቢሮ ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እቅዱን በቀጣይ አምስት ዓመት በርብርብ በመከወን በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ2030 ኤድስን ለማስቆም የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡