ኤጀንሲውን ማጠናከር ለአፍሪካዉያን የተሻሻለ ጤናና መድኃኒት ለማዳረስ ትልቅ ሚና አለው – ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ

ግንቦት 21/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን ማጠናከር ለአፍሪካዉያን የተሻሻለ ጤናና መድኃኒት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን (AMA) በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ሚሼል ሲዲቤ ጋር ተወያይተዋል።

መልዕክተኛዉ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተያዘዉን በመድኃኒቶች ፣ በሕክምና ምርቶችና በተያያዥ ቴክኖሎጂዎች ላይ ዋና ተቆጣጣሪ አካልን የማቋቋም ዕቅድ ለፕሬዝደንቷ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ  በዚህ ወቅት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መማር እንዳሚገባና “ይህንን ተቋም ማደራጀት ለአፍሪካዉያን የተሻሻለ ጤናን እና የመድኃኒት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል” ብለዋል ፡፡

ፕሬዝደንቷ አክለውም “በኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነት ዙሪያ ከታየዉ ብሄርተኝነት እንደምንማረዉ ያሉንን ነባርና እንዲሁም አዳዲስ አህጉራዊ ተቋማትና መዋቅሮች ማጠናከር ይባል” በማለት ገልጸዋል።

እነዚህ ተቋማት ካልተጠናከሩ አህጉሪቷ ለወደፊቱ አደጋዎች ዝግጁ መሆን እንደማትችል አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸውን ከፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።