ኤጀንሲው የመጪው ክረምት የአየር ጠባይ ትንበያን ይፋ አደረገ

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – ብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በበልግ 2013 ዓ.ም ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማ እና በመጪው ክረምት ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እና ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል።
የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታ ትንበያው ኤጀንሲው ከዚህ በፊት ህቶት ከነበረዉ ትንበያ ጋር ተመሣሣይ ነበር ተብሏል።
በዚህም መሠረት ቀጣዩ ክረምት በአብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚጠበቅበት መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ግድቡ በቂ ውሃ የመያዝ አቅም ስለሚኖረው አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ትንበያው አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ሌሎች ግድቦች በቂ ውሃ የመያዝ እድል ይኖራቸዋል ነው የተባለው።
እንደ ሀገር የያዝናቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን የተሳካ ለማድረግ ትንበያው እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ቢሆንም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በመቀነስ ስራዎችን ማከናውን ይኖርብናል ሲሉ የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ አሳስበዋል።
የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው በዘንድሮ የሚጠበቀው የክረምት ዝናብ ኢትዮጵያ በዜጐቿ ጥረት እየገነባች ያለችውን የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን በዝግጅት ላይ በምትገኘበት ወቅት ላይ መሆኑ ትንበያው የተለየ ትርጉም ይኖረዋል ያሉ ሲሆን 2ኛ ዙር የውሃ መሌትን እውን ለማድረግ የዘርፉ የውሃ ባለሙያዎች ቀን ከሌት እየተጉ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በክረምቱ ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ መጠን እና ስርጭት ለውሃ ሙሌቱ ዕውን መሆን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
(በሜሮን መስፍን)