ኤጀንሲው 5ኛውን ዙር የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ለማስጀመር መዘጋጀቱን ገለጸ

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ የሚያካሂደውን የይዞታ ማረጋገጥ ለማስጀመር መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡

ኤጀንሲው በሚያካሂደው የይዞታ ማረጋገጥ ሂደት በ10 ክፍለ ከተሞች 25 ቀጣናዎች ውስጥ የሚገኙ ከ22 ሺሕ በላይ ይዞታዎችና ከ40 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በ5 ወራት ውስጥ በመስክና በሰነድ አረጋግጦ በካዳስተር ሥርዓት ለመመዝገብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

ለይዞታ ማረጋገጥ በተመረጡ ቀጣናዎችና ሰፈሮች ውስጥ የሚገኙ ባለይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጥ አዋጁ በመገናኛ ብዙኃን ከተላለፈ ከ15 ቀናት በኋላ የይዞታ ይረጋገጥልኝ ጥያቄያቸውን በክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሚያወጡት ፕሮግራም መሰረት እስከ ጳጉሜ 5/2014 ዓ.ም ቀርበው እንዲያመለክቱ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ኤጀንሲው ባለፋት 9 ዓመታት ለ4 ጊዜ ይዞታ የማረጋገጥ ሥራ ያከናወነ ሲሆን ከ288 ሺሕ በላይ ይዞታዎችንና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አረጋግጦ መዝግቧል፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ