መስከረም 13/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሕወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ጎራ ለይተው የተሰለፉ ታጣቂዎች እርስ በእርስ መገዳደላቸው ተገለፀ።
ሰርጎ በገባባቸው የተለያዩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ሽንፈት አጋጥሞት እየተበታተነ በሚገኘው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አመራሮች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ጎራ ለይተው የተሰለፉ ታጣቂዎች እርስ በእርስ መገዳደላቸው እና የተወሰኑትም ከቡድኑ ተነጥለው መሄዳቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡
የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ሰሞኑን በሁሉም ግንባሮች የደረሰባቸውን ሽንፈት ተከትሎ በምዕራብ ግንባር ከተለያዩ ስፍራዎች የተራረፉ ታጣቂዎችን እንደገና ለማደራጀት ሙከራ ባደረጉበት ስብሰባ፤ ብዙዎች የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላቸውና ዓላማ ለሌለው ጦርነት ዋጋ መክፈል እንደማይፈልጉ መግለጻቸውና አለመግባባት መፍጠሩን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ስብሰባው በአመራሮችም መካከል ከፍተኛ ንትርክና ጭቅጭቅ ያስተናገደ እንደነበር የገለጹት ምንጮቻችን፤ በተለያየ ጎራ በተሰለፉ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት አስር ሰዎች መሞታቸው እንዲሁም ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ስብሰባውን አቋርጠው መሄዳቸው ታውቋል፡፡
ምንጮቻችን እንደገለጹት አሸባሪው ሕወሓት ሰርጎ በገባባቸው የወልዲያና የሰቆጣ አካባቢዎችም ከፍተኛ የተዋጊ ኃይል እጥረት ስላጋጠመው የአካባቢውን ወጣቶች በግዳጅ ወደ ጦርነት ለማስገባት እየሞከረ ነው፡፡
ሃሳቡ ያልተሳካለት ቡድኑ በወጣቶች እንዲሁም በወላጆች ላይ እርምጃ እንወስዳለን በማለት እያስፈራራ ቢሆንም፤ በተቃራኒው በተደራጀ መንገድ ምከታ እየገጠመው መሆኑን ምንጮቻችን አመልክተዋል፡፡
እንደ ምንጮቻችን ከሆነ ሰሞኑን በጠለምት የአካባቢው ሚሊሻዎችና ነዋሪዎች በተደራጀ መንገድ የአሸባሪ ቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግታት የቻሉ ሲሆን፤ 300 የሚደርሱ ታጣቂዎችም ተደምስሰዋል፡፡