ጥቅምት 18/2017 (አዲስ ዋልታ) የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግብፅ በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ጋር ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።
አራት እስራኤላውያን ታጋቾችን በተወሰኑ የፍልስጤም እስረኞች ለመለዋወጥ ለሁለት ቀናት በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ከዚያም ወደ ዘላቂ እርቅ ለመቀየር በ10 ቀናት ውስጥ ድርድር ለማድረግ ሀሳብ አቅርበናል ሲሉ የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ገልጸው ነበር።
አብዛኞቹ የእስራኤል ሚኒስትሮች ለቀረበው ሃሳብ ድጋፍ ቢያደርጉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ሀሳቡን በመቃወማቸው ቴል አቪቭ ስምምነቱን ውድቅ አድርጋለች።
እስራኤል ከ100 በላይ ዜጎቿ አሁንም በጋዛ ሰርጥ በሃማስ በእስር ላይ እንደሚገኙ የምታምን ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት እስራኤል በተጨናነቀ እና ህዝብ በሚበዛበት አካባቢ በፈጸመችው የአየር ድብደባ ምክንያት ተገድለዋል የሚል ስጋትም አላት።
በአሜሪካ፣ በግብፅ እና በኳታር የሚመራው የተኩስ አቁም ስምምነት እና በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እስረኞች እንዲቀያየሩ ለማመቻቸት የተደረገው ጥረት እስካሁን ለጊዜው መቆሙ ታውቋል።