ሐምሌ 16/ 2013 (ዋልታ)- እስራኤል በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ የታዛቢነት ቦታ ማግኘቷን የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ፡፡
የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ያይር «ይህ ቀን የእስራኤልንና የአፍሪካን ግንኙነት የምናከብርበት ቀን ነው» ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ እስራኤል በህብረቱ የታዛቢነት ቦታ ማግኘቷ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ተቀዛቅዞ የቆየውን ግንኙነት የምታድስበት እንዲሁም ከአህጉሩ ብሎም ከህብረቱ አባል ሀገራት ጋር የተለያዩ ስራዎችን የምትሰራበት ይሆናል ብለዋል፡፡
ለዲፕሎማሲያዊ ስኬቱም የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ትብብር እና በህብረቱ አባል ሀገራት የሚገኙ የእስራኤል ኤምባሲዎች ጥረት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
እስራኤል ከ 55 የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ከ46ቱ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ሲሆን ከሞሮኮ እና ሱዳን ጋር አቋርጣ የነበረውን ግንኙነትም ባለፈው አመት ዳግም ማደሷን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡