እስራኤል ከኢትዮጵያ ጎን የምትቆምበት ወሳኝ ወቅት!

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) እስራኤል በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣውን የኢትዮጵያ መንግሥት የምትደግፍበት ጊዜው አሁን መሆኑ ተገለፀ፡፡

ጄሩሳሌም ፖስት ይዞት በወጣው ሐተታ እስራኤል እንደወዳጅ አገር በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የሰላምና ጸጥታ ግንባታ በመደገፍ አጋርነቷን የምታሳይበት ጊዜው አሁን መሆኑን አመልክቷል።

ጸሐፊና የማኅበራዊ አንቂ እንዲሁም በእስራኤል ብቸኛው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቴሌቪዥን የሆነው (IETV channel) ባለቤቱ ፋሲል ለገሰ ሰፊ ሐተታን አስነብቧል፡፡

የኢትዮ-እስራኤል ግንኙነት ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ታሪካዊ መሰረት ያለው እና ከፖለቲካ በላይ መሆኑን ያነሳው ሐተታው፤ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ያሳለፈችውን ችግሮች እንድትፈታ እስራኤል እንደ ወዳጅ አገር ከጎኗ ቆማ አጋርነቷን የምታሳይበት ወቀት አሁን ነው ሲል አረጋግጧል፡፡

ጸሐፊው በመላው ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎችን ለማሰባሰብ አቅዶ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ ኢትዮጵያዊያን ሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር መስፍን ተገኑን ቃለመጠይቅ በማድረግ ሐቲቱን ያዘጋጁ ሲሆን ሊቀመንበሩ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ሮይተርስና አሶሼትድ ፕሬስን የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀ የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ ሲያደርጉ እያየን ነው ብለዋል።

ሊቀመንበሩ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት በርካታ የሀሰት ዜናዎችን ያለ እረፍት በማሰራጨት ላይ ተጠምደዋል ብለዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ባሉ ጠላቶቿ የተቃጣባትን ጥቃት በምትከላከልበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በተለይ እስራኤል እንደ ወዳጅ አገር ብሎም የረጅም ዘመን አጋር ድገፏን ልታሳይ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

እስራኤል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እና በዴሞክራሲዊ መንገድ የተመረጠውን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ የሚፈልጉ አካላትን ድርጊት በመቃወም በሁሉም የድጋፍ መስኮች ኢትዮጵያን በማገዝ አጋርነቷን ልታሳይ እንደሚገባ በመግለጽ አጋርነቱ በወታደራዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውግንናንም ያካትታል ሲሉ አብራርተዋል።

በአሸባሪው ሕወሓት የተፈጸሙት የግድያ፣ የውድመትና የአጥፊነት ተግባራት ከኢትዮጵያውያን አልፎ በኢትዮጵያ ያሉ ቤተ እስራኤላዊያንንም ህይወት የሚነጥቅ እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አሸባሪው በወረራቸው አካባቢዎች ሴቶችን መድፈሩን፣ ንጹሃን ላይ ግድያ መፈጸሙን እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመት ማድረሱን ማረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኖች የጋራ ምርመራ አሸባሪው ሕወሓት በዘር ማጥፋት ክስ መንግሥትን መወንጀሉ ፈጠራ መሆኑን መረጋጡንና ይልቁንም ቡድኑ መከላከያ ሰራዊትን በመውጋት ጦርነት መጀመሩን፤ በወረራቸው አካባቢዎችም በንፁሃን ላይ ግድያ መፈጸሙን በዚሁ ምርመራ ማስታወቁን አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በአረመኔዊ እና በአምባገነን ስርዓት ሲጨቁን መቆየቱን ዓለም የዘነጋው ይመስላል ያሉት መስፍን ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ፣ አጋር አካላትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ወዳጅ አገር እስራኤል የአሸባሪውን ድርጊት በመገንዘብ የሚያወግዙበት ወቅት አሁን ነው ብለዋል፡፡